የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት

“በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን እንግሊዝ አስፈላጊውን ድጋፍ ታደርጋለች።” ሚስተር ጀርሚ ሃንት

“ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውሕደት እንዲመሠረት ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገሮች ጋር በቅርበትና በትብብር እየሠራች ነዉ።” አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 25/2011ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከእንግሊዝ አቻቸዉ ጀርሚ ሃንት ጋር በሁለትዮሽ እና ቀጠናዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በለውጥና በዴሞክራሲ ግንባታ ሂደት ላይ የምትገኝ መሆኑን አብራርተዉ እንግሊዝ እያደረገች ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍም አድንቀዋል።

ኢትዮጵያ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን በስፋት እየተንቀሳቀሰቸ እንደምትገኝ የገለጹት ሚንስትሩ አቶ ገዱ ከኤርትራ ጋር ስለተደረስው የሰላም ስምምነትም ገለጻ አድርገዋል። በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗንም አብራርተዋል።ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውሕደት እንዲመሠረት ኢትዮጵያ ከአካባቢው አገሮች ጋር በቅርበትና በትብብር እየሠራች ትገኛለችም ብለዋል።
እንግሊዝ በኢትዮጵያ በንግድ እና በኢንቨስትመንት ያላትን ጉልህ ድርሻ አጠናክራ እንደምትቀጥል ሙሉ እምነታቸው መሆኑንም ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጀርሚ ሃንት ደግሞ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እየወሰደች ያለውን ቆራጥ የለውጥ (ሪፎርም) ሂደት አድንቀዉ እንግሊዝ ሙሉ ድጋፏን ትሰጣለች ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ እውን እንዲሆን እንግሊዝ የዲሞክራሲ ተቋማትን አቅም በማሳደግ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግም አረጋግጠዋል።ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በአካባቢው ሰላም እንዲስፍን እያደረገች ያለውን ሰፊ ሥራም አድንቀዉ እንግሊዝ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር መሥራቷን አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል።

እንግሊዝ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ከከፈቱ የዓለም አገሮቸ ውስጥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ እንደምትጠቀስ የገለጹት ሚኒስትሩ ሁለቱ አገሮች በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ እና በባሕል ዘርፍ ጥብቅ የሆነ ግንኙነት አላቸው ነው ያሉት።
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ በለንደን ኤምባሲያቸውን ከከፈቱ የአፍሪካ አገሮች ውስጥ የመጀመሪዋ አገር መሆንዋንም ሚስተር ጀርሚ ሃንት ተናግረዋል፡፡

ምንጭ- የዉጭ ጉዳይ ጽ.ቤት

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *