በልቅሶ ቀናት የሴራ መላምት?

በልቅሶ ቀናት የሴራ መላምት?

Sadik Ahmed

አገር ብሔራዊ ሐዝን ላይ ናት።የሞቱት አባት ናቸው፣የሞቱት ባል ናቸው፣የሞቱት ወንድም ናቸው፣የሞቱት አያት ናቸው። ከሁሉም በላይ የሞቱት እንቁ የሆኑ የአገር ልጆች ናቸው። ነገሮች ምርመራን ይሻሉ። ነገሮች ማጣራትን ይሻሉ። ምርመራው አገር ውስጥ ባሉ መርማሪዎች ካልያም ከውጭ በመጡ ገለልተኛ አጋሮች ሊቃኝ ይችላል። ግዜው የብሔራዊ ሐዘን እንደመሆኑ መጠን ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀድሙ ከፊት ለፊት መምጣት አለበት።

በሰላም ቀጣና በምእራቡ አለም ተቀምጦ ፣ የሴራ ፖለቲካን መላምት አላምጦ ፣ ለአያሌ አመታት መከራ ወደ አጠቃት አገር ውሉ ያልታወቀን መረጃን ማዝነቡ አገሩን ከሚወድ ዜጋ አይጠበቅም። እምዬ ኢትዮጵያ ከዚህ በላይ መሸከም አትችልምና አገር-ወገንን ማረጋጋቱ ይቅደም። አገር-ወገን ሲረጋጋ ፣ ተጠያቂነትን በማንሳት ያለፈው ስንክሳር ምን ነበር? ብሎ ህጋዊ ሒሳብን መተሳሰብ ይቻላል።

በበኩሌ በህዝብ ዘንድና በአለም አቀፋዊ መድረኮች ላይ ተቀባይነቱ እየጎለበተ የመጣው ማእከላዊ መንግስት እራሱን በራሱ ለማናጋት በራሱ ላይ የመፈንቅለ-መንግስት ሙከራ ያደርጋል የሚለውን ትርክት ለመቀበል እቸገራለሁ። የሐሳብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። መቅደም ያለበት ግን ብሔራዊ ጥቅም ነው።

የሴራ እይታዎችን ( conspiracy theories) አቀንቃኝ መሆኑ በአለማችን ላይ አያሌ ማህበረሰቦችን ጎድቷል። ህዝባችንም በዚህ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን። ምእራቡ አለም ላይ ተቀምጠን የምናዥጎደጉደው ሐሳባዊ (imaginary) ምልከታ ‹በሰው ቁስል እንጨት ስደድ› ሊሆን ስለሚችል ‹ባፍ ይጠፉ በለፈለፉ› እንዳይሆን እንጠንቀቅ። በአሰራራችን ላይ ፈጣሪን የመፍራት ፣ ፍጡራንን የማክበር ለከት ይኑረን።

መፈንቅለ መንግስት ሲጠነሰ እንደነበር ድብቅ አልነበረም። ያደባባይ ምስጢር ነው። በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች ፣ በሚዲያ ፣ በየስብሰባው አዳራሽና መሬት ላይ የነበሩት «የበለው ፣ የገፍትረው ፣ የግፋ በለው » … «ጡዘቶች» መች ይዘነጋሉ? የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ «የአብይን ቅያስ መቀልበስ» በሚል ርእስ በመስከረም 20/2010 በጉዳዩ ላይ ለአንባቢያን ጽሁፉን አድርሷል። (የድምጽ ፋይል https://youtu.be/7Za5vLP_EEw) አሁን የሆነው ሆኗል። አገርና ወገን ተፈትኗል። ቢያንስ በሐዘን ቀናቶች ውስጥ የሴራ ትርክቶችን በመቀነስ ለሟች ቤተሰቦችና በሐዘን ለተመታው ወገናችን አክብሮታችን እናሳይ።

ኢትዮጵያ ትፈተናለች ፤ ፈተናንም ታልፋለች!
ልብ ያለው ልብ ይበል!

በሐዘን ወቅት ስድብን ለማዥጎድጎድ የሚመጣ ከሰውኛ ሚዛን ላይ ያፈነገጠ ስለሚሆን የብሎክ ሽልማት ይኖረዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *