አቶ ጌታቸው አሰፋ ተከሰሱ።

⬆️
አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ!

ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች ላይ፤ በማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራው መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ሲካሔድ የነበረው የወንጀል ምርመራ ሲካሔድ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ መሰረት ዓቃቤ ሕግ በወንጀል መርማሪዎች ላይ፤ በማረሚያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በሶስት የተለያዩ መዝገቦች ክስ ተመስርቷ፡፡ በመርማሪዎች ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተከፈተው እና በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በነበሩት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከፈቱት መዛግብት የከስ ሂደቱ ቀጥሎ ምስክር ለመስማት ተቀጥረዋል፡፡

በሶስተኛውና በዚህኛው የመጨረሻ መዝገብ ላይ 26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች በጠቅላላው 46 ክሶች ተመስርቶባቸዋል፡፡ በክሶቹ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ በሌላ በኩል የቀድሞ የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሠፋ በላይ እና አቶ ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የአገልግሎቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በሌሉበት ክስ ዛሬ ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዴታ ምድብ ችሎት ይመሰረትባችዋል፡፡

በአቶ ጌታቸው ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

በሌሎቹ ሁሉም ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ተከሳሾች በግልጽ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፈው በመስራት እንዲሁም ሥልጣናቸው ወይም ኃላፊነታቸው የማይፈቅድላቸውን በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖራቸው በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ በተበዳዮች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸማቸው ነው፡፡

በአቶ ጌታቸው ላይ በንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው
1ኛ) በሚኒስትር ማዕረግ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል የነበሩ በመሆናቸው የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃቸው ከፍተኛ በመሆኑ፤
2ኛ) ኃላፊነታቸውን የጣሱበት ዓላማ ከባድ በመሆኑ እንዲሁም
3ኛ) በሕዝቦች ወይም በተጎጂዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ የተፈጸመውን ወንጀል ከባድ ሊያደርገው በመቻሉ ነው፡፡

ቀሪዎቹ ተከሳሾች በሙሉ በንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ከላይ ለአቶ ጌታቸው ወንጀል ከባድነት ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ተሟልቶ በመገኘቱ ነው፡፡

አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በአራቱ ተከሳሾች ላይ በሌሉበት ክስ ሊመሰረት የቻለው ደግሞ በወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 42/1/ለ እና 161/2/ሀ መሰረት ተከሳሾች የቀረቡባቸው ክሶች ከባድ በመሆናቸው በህጉ መሰረት በሌሉበት ክስ ሊቀርብባቸው የሚገባ በመሆኑ ነው፡፡

ከኢፌዲሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ፣
ቀን ፡- 29 ሚያዚያ 2011 ዓ.ም
አዲስ አበባ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *