አስገራሚው ሰው።

በዚህ አመት ግንቦት ወር ላይ በተባበሩት መንግስታት የፓፓዋ ኒው ጊኒ “Papua New Guinea” ቋሚ ተወካይ በመሆን የተሾሙት ግለሰብ ስማቸው “Max Hufanen Rai” ይባላል። እ.አ.አ. በ1954 ዓ.ም የተወለዱ ሲሆን ዛሬ ላይ የ63 ዓመት ጎልማሳና የስድስት ልጆች አባት ናቸው። በካንቤራ (Canberra) ከሚገኘው የአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ “Australian National University” በዓለም አቀፍ ሕግ (International Law) የተመረቁ ሲሆን ከፓፓዋ ጊኒ ዩኒቨርሲቲ (University of Papua Guinea) ደግሞ በመጀመሪያ ድግሪ (Bachler of Arts) ተመርቀዋል።

“Mr. Rai” እ.አ.አ. ከ1997 እስከ 2003 ዓ.ም ድረስ በ“Federated States of Micronesia” እና “Marshal Islands”፣ እንዲሁም ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም ደግሞ በቻይና የሀገሪቱ አምባሳደር በመሆን አገልግለዋል። በ2013 የፓፓዋ ጊኒ የማዕድን ሚኒስትር ዋና ፀኃፊና አማካሪ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን ከ2014 እስከ 2016 ዓ.ም ደግሞ የሀገሪቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዋና ዳይሬክተር (Director General) በመሆን አገልግለዋል። በመጨረሻም፣ እ.አ.አ. በ2017 ግንቦት ወር ላይ በተባበሩት መንግስታት የሀገሪቱ ቋሚ መልክተኛ ሆነው ተሾመዋል።

በፎቶው ላይ እንደሚታየው “Mr. Rai” በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ የተገኙት ከሞላ ጎደል እርቃናቸውን ነው። በኒውዮርክ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚገኙ የዓለም ሀገራት ተወካዮች በ”Mr. Rai” አለባበስ ከመጠን ያለፈ አግራሞት ውስጥ ገብተው እንደነበር ዘገባዎች ያስረዳሉ።

በእርግጥ ለብዙዎች የአምባሳደሩ አለባበስ ግርምትን ሊፈጥር ይችላል። ነገር ግን፣ አንድ ሰው ከብዙ ሰዎች ጋር አብሮ የተነሳውን ፎቶ ብትሰጡት በመጀመሪያ በዓይኑ የሚፈልገው የራሱን ፊት ሲሆን ቀጥሎ ደግሞ የሚያውቀውን ሰው ነው። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስብሰባ አዳራሽ ማለት የዓለም ህዝቦች በጋራ የተነሱት ፎቶ እንደማለት ነው። የአብዛኞቻችን ተወካዮች በቋንቋም ሆነ በአለባበስ ራሳቸውን ወይም ሕዝባቸውን አይመስሉም። ከሞላ-ጎደል ሁሉም ማለት ይቻላል ከራሳቸው ይልቅ አውሮፓዊያን መስለው ነው በቦታው የሚገኙት። የፓፓዋ ጊኒ ተወካይ ግን ራሳቸው በእውን የሆኑትንና የወከሉት ማህብረሰብ መስለው ነው በስብሰባው አዳራሽ የተገኙት። ለዚህ ነው የዙሉ ጎሳ (Zulu) ተወካዮች በተባበሩት መንግስታት የደቡብ አፍሪካ ተወካይ የሆኑት አምባሳደር እንደ ፓፓዋ ጊኒ ተወካይ ራሳቸውን ሆነው፥ እኛን መስለው ይገቡ ዘንድ ጥያቄ ያቀረቡት።

በፓፓዋ ኒው ጊኒ (Papua New Guinea) የሚገኝ ማህብረሰብ ባህላዊ አለባበስ

አንዳንድ ሰዎች በተባበሩት መንግስታት የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንዲህ ያለ አለባበስ ተገቢ እንዳልሆነ አስተያየት ሲሰጡ ይስተዋላል። ነገር ግን፣ እንዲህ ያለ አስተያየት “አምባሳደሩ ለምን እኛን አልመሰለም?” ከሚል የራስ-ወዳድነት ስሜት የመነጨ እንኳን አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ እኛ የራሳችንን ባህልና እሴት ረስተንና ትተን፣ የምዕራባዊያን ባህልና እሴትን ትክክለኛና ተቀባይነት ያለው አድርጎ ከማሰብ የመነጨ ነው። ስለዚህ፣ የግለሰቡን አለባበስ የሚነቅፉ አስተያየቶች ከራስ-ወዳድነት ይልቅ “አምባሳደሩ ለምን አውሮፓዊያንን አልመሰለም?” ከሚል የአስተሳሰብ ባርነት (conceptual colonization) የመነጨ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።
በአጠቃላይ፣ የአምባሳደሩ አለባበስ የራሱንና የሚወክለውን ሕዝብ ባህልና እሴት የሚያንፀባርቅ ነው። በአጠቃላይ “Mr. Rai” በአለባበሱ የገለፀው ራሱን ነው። ስለዚህ፣ በተባበሩት መንግስታት የሀገሪቱ ቋሚ ተወካይ ሆኖ ወደ ኒውዮርክ ሲሄድ ሌሎችን መስሎ ሳይሆን ራሱን ሆኖ ነው። አንድ ሰው ራሱን ለመሆን የተለየ ቦታና ግዜ መምረጥ የለበትም። እያንዳንዱ ሰው ሁልግዜ ራሱን መሆን መቻል አለበት። መቼም፥ የትም ቢሆን ሰው የሆነውን ሲሆን፥ የሆነው ሲመስል ደስ ይላል። በተቃራኒው፣ በግድ እኛን ምሰል ማለት፥ ሌሎችን መስሎ መገኘት፣ በዓለም ላይ ለተፈጠሩ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች ዋና ምክንያት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *