ሕገ-ወጥ ንግዱ ለፋሲካ በዓል ለእርድ በሚሆኑ የቁም እንስሳት

ሕገ-ወጥ ንግዱ ለፋሲካ በዓል ለእርድ በሚሆኑ የቁም እንስሳት ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳስከተለባቸው የወልድያ ከተማ ሸማቾች እና ነጋዴዎች አስታወቁ፡፡የወልድያ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ደግሞ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ለመያዝ የኬላ ፍተሻ እያካሄደ ጭምር መሆኑን አስታውቋል፡፡

ይህኑን ምክንያት በማድረግ የመተጋገዝ፣ የአብሮነት መገለጫ ተደርጎ የሚጠቀሰውን ለቅርጫ የሚሆን በሬ ለመግዛት ገበያ ያገኘናቸው አቶ ሰይፉ ሞገስ የበሬ ዋጋ ከአምናው የበዓል ዋጋ ጋር ሲያነጻጽሩት ከ10 እስከ 15ሺህ ብር ጭማሪ እንዳለው ነግረውናል፡፡ የበግና የፍየል ዋጋም እስከ 2ሺህ ብር የዋጋ ጭማሪ ማሳያቱን ነው አቶ ሰይፉ የገለጹት፡፡ባደረግነው የገበያ ቅኝትም መካከለኛ በሬ ከ15 አስከ 25 ሺህ ብር፣ ትልቅ በሬ እስከ 45 ሺህ ብር እየተሸጠ ነው፡፡ የበግ ዋጋ ከ1ሺ 500 እስከ 6ሺህ ብር ባለው መካከል ነው፡፡በበሬ ንግድ የተሰማሩት አቶ ይመር ኃይሉ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች በመበራከታቸው እና የሚደረገው ቁጥጥርና እና ክትትል አነስተኛ መሆን ለዋጋ መናሩ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአካባቢው አድልቦ ለመሸጥ የመኖ እጥረትና የፉርሽካ ዋጋ መወደድ በመኖሩ ለእርድ የሚሆኑ እንስሳት ርቀት ካለው ቦታ መምጣታቸው ለዋጋ ጭማሪው አስተዋጽኦ ማድረጉም ተነግሯል፡፡የወልድያ ከተማ ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሰፋ መስፍን የዋጋ ንረት መኖሩን ገልጸው ለዋጋ ንረቱ ምክንያት የሆኑትን ሕገ-ወጥ ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር ሁለት የፍተሻ ኬላዎችን በማቋቋም ወደ ሥራ እንደተገባ አመልክተዋል፡፡ ‹‹ለቁጥጥርና ክትትል ሁሉም ባለሙያዎች ስምሪት ላይ ናቸው›› ያሉት ኃላፊው በዓሉን ምክንያት አድርገው ሕገ-ወጥ ንግድ የሚያከናውኑ ግለሰቦች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ባለ ዓለምዬ -ከወልድያ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *