የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር

‹‹የአዲስ አበባ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ‹የቤልት ኤንድ ሮድ› ተነሳሽነት ሀገራትን የማገናኘት መርህ ማሳያ ነው፡፡›› – ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አህመድባሕር ዳር፡ ሚያዝያ 18/2011ዓ.ም (አብመድ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በቻይና በሁለተኛው ‹የቤልት ኤንድ ሮድ› ዓለም አቀፋዊ ትብብር ጉባኤ መክፈቻ ላይ እየተካፈሉ ነው። በጉባኤው ላይ በዚህ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ውስጥ የሚገኙ ሀገራት መሪዎችም እየተሳተፉ ነው፡፡

በመክፈቻው ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ‹‹የአዲስ አበባ ጅቡቲ የባቡር መስመር በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ግንኙነት ያሳለጠ የቤልት ኤንድ ሮድ ተነሳሽነት ሀገራትን የማገናኘት መርህ ማሳያ ነው›› ብለዋል።
በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለውን ኢንቨስትመንት መር የኢኮኖሚ ፖሊሲና የኢኮኖሚ ማሻሻያ በማስረዳትም ኢንቨስተሮች አዲስ በተከፈቱ ዘርፎች ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈስሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ቻይና ለኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የንግድ አጋር ስትሆን ዋነኛ የቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ምንጭም ናት።ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ በዚሁ የቻይና ጉብኝታቸው ወቅትም ሁለቱ ሀገራ ለቤልት ኤንድ ሮድ ማዕቀፍ የአምስት ዓመት ትብብር እቅድ እና የቻይና አፍሪካ የትብብር መድረክ ስር የሚካሄድ ትብብር መተግበሪያ መግባቢያ ሰነድ ላይ መፈራረማቸው ታውቋል፡፡ 
የቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭ በአውሮፓውያ 2013 በቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ አማካኝነት መተግበር የጀመረ ነው፤ በ2017 የመጀመሪያ ፎረሙን አካሂዷል።

ኢኒሼቲቩ የአፍሪካን ጨምሮ፣ የደቡብ ምሥራቅ እስያን እና የአውሮፓ ሀገራትን ያካተተና ሀገራትን በመንገድና በመሠረተ ልማት የማስተሳሰር ዓላማን ያነገበ መሆኑ ይነገራል።ከ65 በላይ ሀገራትን ያቀፈው ይህ ኢኒሼቲቭ ለቀጠናዊ ትስስር ቅድሚያ በመስጠት የሚሠራም ነው።የፖሊሲ፣ መሠረተ ልማት፣ ንግድ ፋይናንስ እና የሕዝብ ለሕዝብ ትብብርን መሠረት ያደረገ የትብብር ማዕቀፍም ነው።
ምንጭ፡- ኤፍ ቢ ሲ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *